Views: 0
የካቲት 29/2018 ዓ.ም (ኢቴ ቢሮ)
የዲላ ዩኒቨርሲቲ እስቴም ማዕከል በሳምንቱ መጨረሻ (ቅዳሜና እሁድ) መርሐ ግብር ስልጠና ለሚወስዱ ተማሪዎች ገለፃ አድርጓል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ሀብታሙ ተመስጌን (ዶ/ር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የዩኒቨርሲቲው ስቴም ማዕከል ሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ማዕከላት ውጤታማ በመሆን ተሸላሚ የሆኑ ተማሪዎችን ያፈራ ማዕከል መሆኑን አውስተው፣ በቀጣይ ጊዜያት ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ረገድ ከሰልጣኞች ብዙ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
የስቴም ማዕከላት፣ የማህበረሰብን ድካም ከማቅለል አኳያ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ ሰልጣኞች በዩኒቨርሲቲው የሚኖራቸው ቆይታ ያማረ ሆኖ ወደፊት በሀገራችን በሚከፈተው ኤአይ (AI) ዩኒቨርሲቲ ጭምር እንዲቀላቀሉ ምኞታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ግንኙነትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አዲሱ ፍርንጆ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ማዕከሉ በተለያዩ መርሐግብሮች ተማሪዎችን እየተቀበለ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ አውስተው፣ በዛሬው ዕለትም አዲስ ለገቡ 60 የቅዳሜና እሁድ መርሐግብር ሰልጣኞች ቅበላ በማድረግ ገለፃ መደረጉን ገልጸዋል።
ዶ/ር አዲሱ አያይዘውም፣ ሰልጣኝ ተማሪዎች ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ለሀገር የሚጠቅም የፈጠራ ስራ ለመስራት ጠንካራ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የዲላ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ተወካይ አቶ አቤኔዘር አየለ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስቴም ማዕከል የሳይንስና ፈጠራ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች በማሰልጠን በከተማው ላይ የሰራቸው ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ስልጠናው የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት ስለሚያግዝ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
በቅዳሜና እሁድ መርሐ ግብር በዲላ ዩኒቨርሲቲ ስቴም ማዕከል የሚሰለጥኑ ተማሪዎች እስከ ሰኔ 30 ድረስ ስልጠናውን እንደሚወስዱ በመድረኩ ተገልጿል።