Views: 1
ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (ኢቴ ቢሮ)
የካራት ክላስተር ተስፋ ብርሃን የብልፅግና ፓርቲ ህብረት “ጠንካራ አደረጃጀት ለተሳካ ምርጫ” በሚል መሪ ቃል 3ኛ ሩብ ዓመት የአባላት ኮንፈረንስ አካሂዷል።በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የካራት ክላስተር ተስፋ ብርሃን የብልፅግና ፓርቲ ህብረት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘላለም ጳውሎስ፣ ፓርቲው ሥነ-ምግባርን የተላበሱና የተደራጁ አባላትን በመገንባት 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ለማሳለፍ በተጠናከረ ሁኔታ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ዘላለም አክለውም መሠረቱ የጠነከረ የፓርቲ አደረጃጀት ለምርጫ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ አባላት የዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀማቸውን በማጠናከር የፓርቲውን አላማና ፕሮግራሞች በስፋት ማስተዋወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። በኮንፈረንሱ ላይ የቀረበው የ9 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት፣ የካራት ክላስተር ተስፋ ብርሃን የብልፅግና ፓርቲ ህብረት በተለያዩ ዘርፎች ጠንካራ ተግባራትን ማከናወኑን ያሳየ ሲሆን፣ በተለይም ማህበረሰብ ተኮር ሥራዎች በስፋት መከናወናቸው ተመላክቷል።በተጨማሪም 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን የአባላት ጠንካራ ተሳትፎና አደረጃጀት ወሳኝ መሆኑ ተጠቅሶ፣ የፓርቲውን ውግንና በማጠናከር የቅስቀሳ ሥራዎችን በቅርበት መደገፍ፣ መከታተልና በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ ተገልጿል።አባላቱ በማህበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የፓርቲውን የምርጫ ምልክት በማስተዋወቅና በማጋራት ለቅስቀሳ ሥራው አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀርቧል።
እንዲሁም አፍራሽ አጀንዳዎችን በመለየትና የህዝብ ድምፅ በመሆን አዎንታዊ መልዕክቶችን በሚዲያ በማሰራጨት አባላቱ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አቶ ዘላለም ጳውሎስ አሳስበዋል።የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ምክትል እና የቢሮው የብልጽግና ቤተሰብ ሰብሳቢ አቶ ተካልኝ ጌታሁን በበኩላቸው፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ ክልል ሆኖ ከተደራጀ በኋላ ታሪካዊው 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ይህ ምርጫ ለክልሉ ህዝብ የታሪክ ምዕራፍ ሲሆን፣ በዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ውስጥ የህዝብ ተሳትፎን የሚያጠናክር እና የክልሉን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ወደ አዲስ ደረጃ የሚያሸጋግር እንደሆነ አቶ ተካልኝ ተናግረዋል።የህብረቱ አባላት በዚህ ታሪካዊ ምርጫ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሁሉም አካላት በአንድነትና በንቃት በመሳተፍ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊውን ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።